copticcast
copticcast 29 Feb 2020
1

Up next

Deal or No Deal Series Part 3: Call No Man Father
01 Oct 2020
Deal or No Deal Series Part 3: Call No Man Father
copticcast · 1 Views

ቅዱስ ስምኦን (ጫማ ሰፊው) - ክፍል 2 / Saint Simon - Part 2

8 Views

ቅዱስ ስምኦን (ጫማ ሰፊው
ተአምረ ማርያም ላይ ከተጻፉት እና በትርጓሜ ወንጌልም ላይ በማቴ5÷29 ለሚገኘው ቃል እንደ ታሪካዊ ማስረጃ ከሚቀርቡት ታሪኮች አንዱ የስምዖን ጫማ ሰፊው ታሪክ ነው፡፡
በ979 ዓም የፋጢማይድ ሥርወ መንግሥት ግብጽን በሚያስተዳድርበት ወቅት በከሊፋ አል ሙኢዝ ሊ ዲን ኢላህ አል ፋጢሚ ዘመን እንዲህ ሆነ፡፡

ለሥልጣን ሲል ወደ እስልምና የተቀየረ ያዕቆብ ኢቢን ቂሊስ የሚባል አንድ አይሁዳዊ ነበር፡፡ ይህ አይሁዳዊ ምንም እንኳን ለሥልጣን ሲል እስልምናን ቢቀበልም ልቡ ግን ከአይሁድ ጋር ነበር፡፡ ክርስቲያኖችንም በጣም ይጠላ ነበር፡፡ ይህ ጥላቻው የመጣው በከሊፋው ዘንድ በሚወደድ እና እርሱ ይቀናቀነኛል ብሎ በሚያስበው በአንድ ክርስቲያን ምክንያት ነበር፡፡ ይህ ክርስቲያን ቁዝማን ኢቢን ሚና ይባል ነበር፡፡
ከሊፋ አል ሙኢዝ ደግ፣ ምክንያታዊ እና በሰዎች ነጻነት የሚያምን ዕውቀትንም የሚወድድ መሪ ነበር ይባላል፡፡ ምሁራን ሲከራከሩ መስማት የሚወድድ ሌላው ቀርቶ የእስልምና ምሁራን እስልምናን ከሚቃወሙ ሰዎች ጋር በነጻነት እንዲከራከሩ የሚፈቅድ ሰው ነበረ፡፡

ይህንን ጠባዩን የሚያውቀው ያዕቆብ ሙሴ የተባለውን የአይሁድ ረቢ ጠርቶ ከፓትርያርኩ ጋር እንዲከራከር እና ፓትርያርኩን እንዲያሳፍረው መከረው፡፡ ሙሴም ጥያቄውን ለከሊፋው አቀረበ፡፡ ከሊፋውም ለፓትርያርኩ መልእክት ላከ፡፡
በቀጠሮው ቀን በወቅቱ የእስክንድርያ ፓትርያርክ የነበረው አብርሃም ሶርያዊ በሃይማኖት ዕውቀቱ እና ትምህርቱ የታወቀውን ሳዊሮስ ዘእስሙናይን ይዞት መጣ፡፡ ሳዊሮስ ዘእስሙናይ «በከሊፋው ፊት ይሁዲን መናገር መልካም አይደለም» አለው፡፡
ይህንን ቋንቋ ሙሴ በሌላ ተርጉሞ «አላዋቂ ብለህ ሰደብከኝ» ሲል ተቆጣ፡፡
ከሊፋ አል ሙኢዝም «መከራከር እንጂ መቆጣት አያስፈልግህም» አለው፡፡
ያን ጊዜ ሳዊሮስ «አላዋቂ ብዬ የተናገርኩህ እኔ ሳልሆን ያንተው ነቢይ ኢሳይያስ ነው» ብሎ በትንቢተ ኢሳይያስ 1÷3 ላይ ያለውን ጠቀሰ፡፡ ከሊፋው ገረመውና «እንዲህ የሚል የእናንተ ነቢይ አለ?» ሲል ሙሴን ጠየቀው፡፡ ሙሴም «አዎ አለ» አለው፡፡ አባ ሳዊሮስም «እንዲያውም እንስሳት ከአንተ እንደሚሻሉም ገልጧል» አለው፡፡ ይሄን ጊዜ ከሊፋው ሳቀ፡፡ ክርክሩም እንዲቆም አዘዘ፡፡
ይህ ሁኔታ ያዕቆብን አበሳጨው፡፡ ራሱ ባመጣው ጣጣ በከሊፋው ፊት መዋረዱም ቆጨው፡፡ ስለዚህም ክርስቲያኖቹን የሚያጠቃበት ሌላ መንገድ መፈለግ ጀመረ፡፡ ሙሴንም አንዳች ጥቅስ ከወንጌል እንዲፈልግ ነገረው፡፡

ሙሴ በመጨረሻ በማቴ 17÷20 ያለውን «የስናፍጭ ቅንጣት ታህል እምነት ቢኖራችሁ ይህንን ተራራ ከዚህ ተነሣ ብትሉት ይሆናል» የሚለውን አገኘ፡፡ ለያዕቆብም ነገረው፡፡ ያዕቆብም ወደ ከሊፋው በማምጣት «በክርስቲያኖች መጽሐፍ ላይ እንዲህ ስለሚል ይህንን ፓትርያርኩ ያሳየን» አለው፡፡ ከሊፋው ተገረመ፡፡ ፓትርያርኩንም ጠርቶ ጠየቀው፡፡ አብርሃም ሶርያዊ ይህ ቃል በእውነት እንዳለ ነገረው፡፡
ከሊፋውም «በእውነት የክርስቲያኖች ሃይማኖት እውነት ይሁን ውሸት ለመፈተኛ ይህ ጥሩ አጋጣሚ ነው፡፡ ይህንን ማድረግ ካቃታቸው ግን ሕዝቡን እያታለሉ ነውና መቀጣት አለባቸው» ብሎ አሰበ፡፡
ከሊፋ አል ሙኢዝ ለአባ አብርሃም አራት ምርጫ አቀረበለት

1. የሙካተምን ተራራ ከምዕራብ ወደ ምሥራቅ ማዛወር ወይም
2. እስልምናን ተቀብሎ ክርስትናን መተው ወይም
3. ግብጽን ትቶ ወደ ሌላ ሀገር መሄድ ወይንም
4. በሰይፍ መጥፋት

ፓትርያርክ አብርሃም ውሳኔውን ለማሳወቅ የሦስት ቀን ጊዜ ጠየቀ፡፡ ከከሊፋው ዘንድ ከወጣ በኋላም ጳጳሳቱን፣ መነኮሳቱን፣ ካህናቱን፣ ዲያቆናቱን እና ምእመናኑን ሰበሰበ፡፡ ያጋጠመውንም ነገር ነግሮ በመላዋ ግብጽ የሦስት ቀን ጾም እና ጸሎት አወጀ፡፡

በሦስተኛው ቀን ማለዳ ቅድስት ድንግል ማርያም ለአባ አብርሃም ሶርያዊ ተገለጠችለት፡፡ «ይህንን ነገር የሚያደርግልህ አንድ ሰው አለ፡፡ ወደ ከተማው ገበያ ስትወጣ አንድ ዓይና የሆነ በገንቦ ውኃ የተሸከመ ሰው ታገኛለህ፡፡ እርሱ ይህንን ተአምር ያደርግልሃል» አለቺው፡፡
አባ አብርሃም ወዲያው ከመንበረ ጵጵስናው ወጥቶ ወደ ከተማው ገበያ መንገድ ጀመረ፡፡ በመካከሉም አንድ በገንቦ ውኃ የያዘ ሰው አገኘ፡፡ ያም ሰው አንድ ዓይና ነበረ፡፡ ጠራውና ወደ ግቢው አስገባው፡፡ የሆነውንም ነገረው፡፡
ያ ሰው «እኔ ኃጢአተኛ ነኝ፤ ይህ እንዴት ይቻለኛል» አለው፡፡
አባ አብርሃምም ያዘዘቺው ድንግል ማርያም መሆንዋን ነገረው፡፡
ያ ሰው ስምዖን ጫማ ሰፊው ይባላል፡፡ አንዲት ሴት እየደጋገመች መጥታ «ይህንን ዓይንህን እወድደዋለሁ» ብትለው ጫማ በሚደፋበት ጉጠት አውጥቶ የሰጣት እርሱ ነው፡፡

«አባቴ ሕዝቡን ወደ ተራራው ሰብስብ፡፡ እኔ ከአንተ አጠገብ እሆናለሁ፡፡ በአራቱም አቅጣጫ አንድ መቶ አንድ መቶ ጊዜ ኪርያላይሶን በሉ፡፡ ከዚያም ስገዱ፡፡ ከስግደቱ በኋላ ስታማትብ ተራራው ይነሣል » አለው፡፡
አባ አብርሃም ወደ ከሊፋው ሄዶ ተራራውን እንደሚያነሡት ነገረው፡፡

ኅዳር 15 ቀን 975 ዓም ሙስሊሞች፣ ክርስቲያኖች፣ አይሁድ፣ ሌሎችም ተሰበሰቡ፡፡ በአራቱም አቅጣጫ ጸሎተ ዕጣን ተደርሶ ኪርያላይሶን ተባለ፡፡ ከዚያም ሕዝቡ ሁሉ ሰገዱ፡፡ ከስግደት ተነሥተው ጸጥ ሲሉ ኃይለኛ ድምፅ ተሰማና ተራራው ካለበት ተነሣ፤ ፈቀቅም አለ፡፡ እንደገና ሰገዱ፤ አሁንም ተነሥቶ ፈቀቅ አለ፡፡ ለሦስተኛ ጊዜ ሰገዱ ተነሥቶ ወደ ምሥራቅ ሄደ፡፡ በዚህ ጊዜ ከሊፋው በከፍተኛ ድምፅ ጮኸ፡፡ «በቃ፣ በቃ በዚህ ከቀጠለ ከተማዋ ትፈርሳለች» አለ፡፡ ክርስቲያኖቹ በደስታ አምላካቸውን አመሰገኑ፡፡ ከሳሾቻቸው አፈሩ፡፡ ስምዖን ጫማ ሰፊው ግን ጠፋ፡፡
አባ አብርሃም በብርቱ አስፈለገው፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ሊያገኘው አልቻለም፡፡ አባ አብርሃም ሶርያዊ ይህንን የድንግል ማርያምን ተአምር ለማስታወስ ከነቢያት ጾም ጋር ተያይዞ እንዲጾም አዘዘ፡፡ በገና ጾም የመጀመርያዎቹ ሦስት ቀናት ይህንን ተአምር ለማስታወስ የምንጾማቸው ናቸው፡፡
ዛሬ ተራራው ከሦስት ቦታ ተከፍሎ ይታያል፡፡ ከምዕራብም ወደ ምሥራቅ ሸሽቷል፡፡ «ሙከተም» ማለትም «የተቆራረጠ» ማለት ነው ይባላል፡፡ ይህ ተራራ ዛሬ በአሮጌዋ ካይሮ ይገኛል፡፡

ከዚህ ተአምር በኋላ ከሊፋ አል ሙኢዝ ለቤተ ክርስቲያን ብዙ ነገር አድርጓል፡፡ አያሌ የፈረሱ አብያተ ክርስቲያናት ተጠግነዋል፡፡ አዳዲሶቹም ተሠርተዋል፡፡ ይህ ተአምር የግብጽ ፓትርያርኮች ታሪክ በተሰኘው ጥንታዊ መጽሐፍ እና በሌሎችም መዛግብት ተመዝግቧል:: በተአምረ ማርያም ላይ የምናገኘው ታሪክ ከእነዚህ ጥንታውያን መዛገብት የተገኘ ነው፡፡ በሌላም በኩል ተራራው እና በአሮጌዋ ካይሮ የመዓልቃ ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን ዙርያ የተደረጉ የአርኬዎሎጂ ቁፋሮዎችም ይህንን መስክረዋል፡፡
በኋላ ግን ቦታው ሆን ተብሎ የካይሮ የቆሻሻ መጣያ ተደረገ፡፡ ክርስቲያኖቹ ወደ አካባቢው የሚጣለውን ቆሻሻ በመጥረግ ታሪኩ እንዳይጠፋ ታገሉ፡፡ በመጨረሻም ነገር ሁሉ ለበጎ ነውና ቆሻሻዎቹን እንደገና ለአገልግሎት በማዋል /ሪሳይክሊንግ/ መጠቀም ጀመሩ፡፡ ዛሬ ለብዙዎች የሥራ እድል ከፍቶላቸዋል፡፡

የአል ሙከተም ተራራ ተፈልፍሎ የስምዖን ጫማ ሰፊው ቤተ ክርስቲያን ተሠርቷል፡፡ የቤተ ክርስቲያኑ መቅደስ ክፍት ነው፡፡ ወንበሩ 25000 ምእመናን ይይዛል፡፡ የስምዖን ዐጽምም በመዓልቃ ቤተ ክርስቲያን በተደረገው ቁፋሮ ተገኝቶ በዚሁ የተራራ ቤተ ክርስቲያን በክብር አርፏል፡፡
----------------------------------------
ዲ.ን ዳንኤል ክብረት

Show more
0 Comments sort Sort By

Up next

Deal or No Deal Series Part 3: Call No Man Father
01 Oct 2020
Deal or No Deal Series Part 3: Call No Man Father
copticcast · 1 Views